ትክክለኛው የቅድስት አርሴማ ስዕል የትኛው ነው? Correct St Arsema icon pic

በብዛት የቅድስት አርሴማ አድርገን የምንጠቀመው ስዕል የሌሎች ሰማዕታትን ስዕል እንደሆነ ያውቃሉ? ስዕላቸው የቅድስት አርሴማ ዘአርማንያ መስሎን የምንጠቀማቸው ቅዱሳን ሰማቸው በዋነኛነት ቅድስት ባርባራ ቅድስት ሉሲያ ቅድስት ኪርያኬ እና ቅድስት ካትሪን ይባላሉ::እነዚህ ሰዎች እንደመፅሃፍ ቅዱስ ቃል እንደ ቅዱሳን ሴቶች ራሳቸውን እንደተከናነቡ መሳል ነበረባቸው ያለምንም አሸንክታብ:: 1ኛ ቆሮ 11፡6፡፡ ነገር ግን የቅድስት አርሴማ ምስል አድርገን መቀበላችን ስህተቱ ሳያንስ እነሱም ቢሆኑ ይሄንን ኦርቶዶክሳዊ ስርዓት አያሟሉም::ቀጥሎ በስህተት አርሴማ መስለውን ስዕላቸውን የምናዛባውን ቅዱሳን ታሪክ እናያለን::

በቅድሚያ ቅድስት አርሴማ ማናት

ቅድስት አርሴማ ከአባቷ ከቅዱስ ቴዎድሮስና ከእናቷ ቅድስት አትናሲያ በስዕለት የተገኘች ናት:: ትውልዷም በ3ኛው መቶ ክፍለዘመን በሃገረ ጣልያን ሮም ሲሆን በሰማዕትነት ያረፈችው በአርመንያ ሀገር እኤአ በጥቅምት 290 ነው:: ስሟ እኛ አርሴማ ስንለው በሌሎች ሂርፕስማ /St Hripsime ይሏታል:: ወደ አርመንያ የተሰደደችው ንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ ድንግል አርሴማን ካላገባው ብሎ በማስቸገሩና ፀረ ክርስትያን በመሆኑ ከሌሎች 27 ክርስቲያኖች ጋር በጎርጎርዮስ ከሳቴ ብርሃን(ለአርመን ክርስቲያን ፋና ወጊ አባት የሚቆጠር ) መሪነት ነው::ጎርጎርዮስም በአርመንያ ገዥ ንጉስ ድርጣድስ ቤት በባርነት ሲቀጠር ቅድስት አርሴማን ይሄም ንጉስ ካላገባሽኝ ሲላት እኔ የስማያዊ ንጉስ ሙሽራ ነኝ አላገባህም ብላ ገፍትራ ጣለችው ተናዶ እሱም አይኗን አወጣው :: ሌሎችም ለጣዖት እንዳይሰግዱ ስታስተምር በመጨረሻም በሰማዕትነት መስከረም 29 ቀን አረፈች:: ከ80 ከመቶ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሆኑባት አርመን ቅድስት አርሴማ የመጀመርያዋ ሰማዕት ተደርጋ ሲቀበሏት ከሷ ጋር ተሰደው በድንግልናቸው ፀንተው ካረፋት ውስጥ እንደ ቅድስት ኒኖ በጎረቤት አገር ጆርጂያ በሰፊው ክብር አላቸው::

ቅድስት አርሴማ በኢትዮጵያውያን አሳሳል

የቅድስት አርሴማ አጽም በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ አባቶቻችን በትውፊት ይናገራሉ ።በጣና ደሴት ጎጃም እንዲሁም በወሎ ሲሪንቃ የሚገኙት አድባራት ለዚሁ ተጠቃሽ ናቸው:: በተለይም ባለንበት ክፍለዘመን ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሃገር ሁሉ ቅድስት አርሴማ ገናና ሰማዕት ሆናለች::

ቅድስት አርሴማ -ንጉስ ድርጣድስ ረግጣ

ትክክለኛው የቅዱሳን ስዕል አሳሳል

ቅዱሳን ስዕል ላይ አክሊል ፅዋ መስቀል ዘንባባ መያዝ የተለመደ ነው:: የህፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ ስዕል ላይም ዘንባባው ፅዋው መስቀሉ ይታያል:: በስእሉ ላይ አንዱ ቢጎድል ስህተት ባይሆንም ሚዲያው ግን ዘንባባ ያየ ሁሉ ቅድስት አርሴማ ይመስለዋል:: በዩቲዩብ የቅድስት አርሴማ መዝሙር ላይ ይሄን ማየት ይቻላል::

ፅዋው ባይኖርም

በደብሯም ሆነ በየምዕመናን ቤት ከሚገኙት ስዕላት በስርጭት ረገድ የቅድስት ባርባራ ስዕል እንደአርሴማ ተደርጎ በመሸጥ ከፍተኛው ነው::ቀጥሎም የቅድስት ሉሲያ ስዕል አልፎአልፎም የቅድስት ካትሪንና የቅድስት ኪርያኬ ስዕልን በስህተት የቅድስት አርሴማ አድርጎ መጠቀም በዝቷል:: እነዚህ ሰማዕታት በውጣትነታችው በድንግልናቸው ጣዖትን ባለማምለካቸው የክርስቶስን መስቀል መከራ በመቀበላቸው ተመሳሳይ ታሪካቸው በስዕላቸው እስከመደናገር ያደረሰን ይመስላል:: ለምሳሌ ሁሉም ሰማዕታት መስቀል ዘንባባ ፅዋ ይዘው በካቶሊክም በኦርቶዶክስም ዘንድ ይሳላሉ:: በሰዕላቱ ላይ

መስቀል የሚይዙት የሚወደኝ ቢኖር መስቀሌን ተሸክሞ ይከተለኝ ባለው ቃል መሰረት የክርስቶስን መስቀል መከራ መቀበላቸውን ያመለክታል:: ሉቃስ 9:23

ፅዋ የሚይዙት የሞትን ፅዋ ስለመቀበላቸው ::ማቴዎስ 26:39

እንዲሁም ዘንባባው አለምን እና ሰይጣንን ድል አድርገው መንግስተሰማያትን በአሸናፊነት ስለመውረሳቸው ለማስረዳት ነው::

ትክክለኛው የቅድስት አርሴማ ስዕል – በሠዓሊ ዘሪሁን ገ/ወልድ

እንደቅዱስ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ ያሉ ሰማዕታት ላይ እንደምንመለከተውም ሰማዕታት አክሊል ሲወርድላቸው ይታያል::እስከሞት ደረስ የታመንክ ሁን የህይወትን አክሊል እሰጥሃለው ብሎ ጌታችን እንዳለ አክሊሉ ሽልማታቸው ነው::ዮሐ ራዕይ 2:10

ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ሲሆን አምልኮተ ጥዖት በበዛበት የአረማውያን ጭካኔን ሳይፈሩ በደማቸው የክርስቶስን አምላክነት ስለመሰከሩ ሥዕላቸው ባብዛኛው ቀይ ቀለም ይበዛዋል:: ያለደም ምስክር የሆኑ ቅዱሳን ቢጫ ልብስ ሲያዘወትሩ ሁሉም ሰማያዊ ቀለም ስለሰማያዊነታቸው ይገባበታል::ቅዱሳን ፊታቸው በሙሉ ይታያል እንጂ በጎን አይሳሉም:: እንደ ይሁዳ ያሉ ወይም ክፋ ሰዎች ግን ግማሽ በጎን የቀኝ ወይ የግራ ፊታቸው ብቻ እንዲታይ ተደርጎ ይሳላል::

በዋነኛነት ትኩረት የሚሰጠው ደሞ ቅዱሳን በሚሳሉበት ወቅትጌጣጌጥ አያስፈልጋቸውም:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሰዎች ምዕራፍ 11 ከቁጥር 4-15እንዳዘዘውም ሴቶች ራሳቸውን ፀጉራቸውን መሸፋፈን አለባቸው:: እንደ ቅድስት አርሴማ አድርገን በስህተት የተቀበልናቸው ስዕላት ውስጥ በተለይ ቅ.ሉሲያ እና ቅ ባርባራ ፀጉራቸው መታየት ብቻ ሳይሆን እስከታች ወርዷል::ይህም በጣልያን አሳሳል ዘይቤ ወጣታዊ ውበታችውን ለማጉላት ይመስላል::ግን እንደ ቅዱሳት አንስት ለመሳል ግን ስጋዊ ማንነታቸው በፀጋ እግዚአብሔር ፀጉራቸው ተሸፍኖ መሳል ነበረበት::

የመጀመሪያው ስህተት የሌሎች ስዕል ላይ አርሴማ እያልን መፃፋችን ሲሆን ሁለተኛው ስህተት ደግሞ ስጋወደሙ በሚፈተትበት ቤተመቅደስ የተገላለጠ ገላ ከኦርቶዶክሳዊ ቀኖና ውጭ እንደቅዱስ ተደርጎ መከበሩ ነው::ሶስተኛም እነዚህ ቅዱሳን ባብዛኛው የካቶሊክ ተከታዮች የሚያከብሯቸው እንጂ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ዶግማን ያሟሉ ቅዱሳን ስለመሆናቸው ማስረጃ መቅረብ አለበት::

ከዚህ ቀጥሎ በስህተት እንደ የቅድስት አርሴማ ስዕል ያሳሳቱን ቅ.ባርባራ ቅ.ሉሲያ ቅ.ካትሪን እና ቅድስት ኬርያኬ ታሪክ ባጭሩ ይቀርባል

ቅድስት ባርባራ:-ባሁኑ አጠራር በአልቤክ ሊባኖስ ሃገር ድሮ ፊንቄ ይባል በነበረ ቦታ ተወለደች::አባቷ ዲዮስቆሮስ ጥዖት አምላኪ የሆነና እሱንም እንድትከተል ሲያስገድዳት እምቢ በማለቷ በገዛ አባቷ በ33 አመቷ በ306 አም ተሰዋች::ቅድስት ድንግል ሰማዕት ተደርጋ በካቶሊክ በምስራቅ ኦርቶዶክሳውያን እና በግብፅ ተቆጠራለች አመታዊ በዓሏ ዴሴምበር 6 ይከበራል:: በስዕሎቿ ላይ የተፃፈው በፅርዕ ቋንቋ «ΗΑΓΙΑ ΒΑΡΒΑΡΑ» የሚለው ሲተረጎም በእንግሊዘኛው SAINT BARBARA በኛ ቅድስት ባርባራ ማለት ነው::አርሴማ አይደለም::

ቅድስት ባርባራ በአባቷ የተገደለች ሰማዕት

ቅድስት ሉሲያ:– የዕዉራን መፅናኛ በመባል የምትታውቅ ሲሆን ክርስቲያን በመሆኗ በመከራ ያወጡባትሁለት አይኖቿን በሰህን ላይ በእጇ ይዛ ተስላ ትታያለች::የአይኑ ታሪክ ከአርሴማ ጋር አንድ አይነት ነው::አርሴማን ወደ አርመንያ ያሳደዳት ንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ ክርስቶስን ካልካድሽ ብሎ በተወለደችበት ጣልያን ሲሲሊ ሲራኮስ በ304 አም በ21 አመቷ እንድትሞት አደረገ::በሮም ካቶሊክ እንደእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልዩ ሁኔታ ከሚያከብሯቸው 8 ቅድሳት አንስት ቅድስት ሉሲያን ሲመድቧት በሉተራውያንም ዘንድ ተቀባይነት አላት::

ቅድስት ሉሲያ የእውራን መፅናኛ ሰማዕት

ቅድስት ካትሪን ዘእስክንድርያ(በፅርዕ ፊደል ΗΑΓΙΑ AIKATEPINH -St Cathrine :-ወላጆቿ ከነገስታት ወገን ሲሆኑ ንጉስ ማክሴንቲየስ ካላገባሁሽ ሲላት እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ ምድራዊ ንግስትነት አልፈልግም ብላ እንደ ቅድስት አርሴማ የመለሰች ድንግል ሰማዕት ናት::በተለይም የልዑላውያን ዘመድ ቅርበት ተጠቅማ መኳንንቱን ሁሉ በእግዚአብሄር እንዲያምኑ ያስተማረች በዚህም በመገረፍ በጋሪ በመጎተት መከራ ደርሶባት በመጨረሻም በ305 አም በለጋ እድሜዋ በ18 አመቷ በሰይፍ ተከለለች::በግብፅ ኮፕቲክ በምስራቅ ኦርቶዶክስና ካቶሊካውያን ዘንድ በድንግልናቸው ለሚፀኑ ወጣቶች አርአያ ናት::

ድንግል ቅድስት ካትሪን

ቅድስት ኬርያኬ:-ክርስቲያን ከሆኑ ግሪካውያን ሃብታም ወላጅ አባቷ ዶሮቴዎስ እናቷ ዮሴብያ በኒቆሞዲያ ተወልዳ ሃብታቸውን ለመውረስ ሲል ለሃገረ ግዥ ልጅ ለትዳር ስትጠየቅ በድንግልነቷ በመፅናቷ መከራ ብዛባት:: ወላጇቿ ተግዘው ሞቱ::የአረማዊው ንጉስ ዲዮቅልጥያኖስ የበታች ሹማምንትን ሁሉ እየተቀባበሉ በጣዖት እንድታመልክ ቢያባብሏትም በእሳት ጥለዋት አላቃጠላትም ለአውሬዎች ተሰጥታ አልበሏትም እምቢ ለሃይማኖቴ ብላ ፀንታ በሰይፍ ልትሰዋ ተዘጋጅታ እያለች በተሰጣት ፀሎት ማድረጊያ ደቂቃ ውስጥ እየፀለየች ነፍሷ ፈጣሪ እጅ ገባች::ቅድስት ኬርያኬ በ21 አመቷ በ289 አም ኬልቄዶን በተባለ ቦታ አረፈች::በዚህም ተአምር የተነሳ ብዙ አረማውያን በቅድስት ኪርያኬ አምላክ እንዲያምኑ ሆኑ::ተመሳሳይ የሰለስቱ ደቂቅን ታሪክ ከምናምን ኦርቶዶክሳውያን ይልቅ በካቶሊካውያን እና እንደ ግሪክ ያሉ መለካውያን ምስራቅ ኦርቶዶክሶች በሙሉ ተቀብለዋት ሃምሌ 6 እና 7 አመታዊ በዓሏን ያከብራሉ::

ቅድስት ኪርያኬ

ለማጠቃለል ያህል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የአንዱን ቅዱሳን ክብር ለሌላው አንስጥ::የኮከብ ክብር አንዱ ካንዱ ይለያል እንደሚል ቅዱስ መፅሃፍ:: በተለይም ያንዱን ስዕል ፍቆ ሌላ የሌላ ስም መፃፍ ሃይማኖታዊ አይደለም:: የስዕል መብት ቅጂንም copy right መጣስ ነው:: የእውራን እናት ተደርጋ የምትውሰደውን ቅድስት ሉሲያን መጽሃፍ ቅዱሳዊ አሳሳል እንድታሟላ ሲሉ ለምሳሌ አንዳንዶች ፀጉሯን የሚሸፍን ፎቶ ኤዲት አድርገው አንዳንዶች ደሞ ሳይሸፈን በሚዲያ ይለጥፋሉ::ከዚሁ ሁሉ ጣጣ ትክክለኛውን ኢትዮጵያዊ ለዛ ያለውን ትክክለኛውን የቅድስት አርሴማን ምስል ብንጠቀም አይሻልም ወይ?

ቅድስት ሉሲያ እንጂ አርሴማ አይደለችም

የጣልያኗ ሰማዕት ሉሲያን በጣም የሚያከብሩ ካቶሊካውያን ለምንድነው አርሴማ ብላችሁ የፃፋችሁባት ቢሉንስ? ለዚያውም ፀጉሯ ሳይሸፈን የተሳለች ሴትን መቀበል ያሳስታል:: ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትም አይደለም መፅሃፍ ቅዱስ እንደሚያዘው ሁሉ በስርዓት ይሁን:: በስህተት የምንጠቀመውን ስዕለ አርሴማ ትተን በኢትዮጵያውያን የተሳሉትን ትክክለኛ ስዕለ አርሴማን እንያዝ:: ለምሳሌ በአዲስ አበባ ማህበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ውስጥ እንዲሁም ቦሌ ሰሚት ቅዱስ ጊዮርጊስ ወአርሴማ ደብር ውስጥ ያገኙታል::

ቅድስት አርሴማ ንጉስ ድርጣድስን አላገባህም ብላ እንደጣለችው

ከሰማዕታቱ በረከት ይክፈለን

ወስብሃት ለእግዚአብሔር

ተፃፈ በዲ አብርሃም ሙኒክ ጀርመን

ምንጭ

Author: mr☻n Ta Αβραάμ

Long live Ethiopia “When dictatorship is a fact, revolution becomes a right." victor Hugo

Leave a comment